(አዲስኒውስ) – ለአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር ፕሮጅክት 41 ባቡሮችን ለመስራት ከኢትዮጲያ መንግስት ጋር ስምምነት የፈጸመውና ካለፈው ግንቦት ጀምሮ ስራውን በማከናውን ላይ የሚገኘው ‘ቻይና ሲ ኤን አር ቻንግቹን ሬልዌይ ቪሄክልስ’ የተባለው የቻይና ባቡር አምራች ኩባንያ የመጀመሪያውን ባቡር ሰርቶ ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ ምድር ባቡር ፕሮጅክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር በሀይሉ ስንታየሁ አስታወቁ፡፡
ዋና ስራ አስኪያጁ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ይህ ስራው የተጠናቀቀው ባቡር በአሁኑ ውቅት በመርከብ እየተጓጓዘ ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ ያለ ሲሆን በወረሃ መስከረም 2007ዓ.ም አጋማሽ አዲስ አበባ ይገባል ብለዋል፡፡
“በዋና ዋና መስመሮች ያለው የሲቪል ግንባታ እና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች እየተጠናቀቁ ነው፡፡” ያሉት ኢንጂነር በሀይሉ ስንታየሁ ለባቡሩ ከተሰራው የሀይል ማግኛው እስከ ላይኛው የባቡሩ ሀይል ማጠራቀሚያ ቋቶቹ ድረሰ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያዎቹ ተከላ በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል፡፡ ስለ ባቡሩ አመጣጥም የተናገሩት ዋና ስራ አስኪያጁ ባቡሮቹ በሶስት ዙር የሚጓጓዙ ሲሆን አሁን በመምጣት ላይ ያለው አንደኛው ዙር ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ምድር ባቡር ፕሮጅክት የህዝብ ግንኙነት ጉዳይ ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ተፈራ በበኩላቸው “በመምጣት ላይ ያለው ባቡር ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የአዲስ ዓመት ገጸ በረከት ነው፡፡” ብለዋል፡፡
China CNR Changchun Railway Vehicles Company building new light trains for Addis Ababa
በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት ዕጥረት ይቀርፋል ተብሎ በመንግሰት ከተያዙት መፍትሔዎች አንዱ የሆነው የከተማው ቀላል የባቡር መስመር መዝርጋት ከተጀመረ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በእስካሁኑም ከፍተኛ የሆነ ስራ እየተሰራ ሲሆን በከተማው ለመስራት በታሰበው 32 ኪሎ ሜትሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሲቪል እና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ የገለጹት አቶ ደረጅ ተፈራ የባቡሩን የግንባታ ሁኔታ ሲገልጹ ከቃሊቲ በሳሪስ አድርጎ መስቀል አደባባይ የሚዘረገው መስመር የሀዲድ ዝርጋታው ተጠናቅቆ ተጨማሪ የኤሌክትሮ ሚካኒካል ስራዎች በመሰራት ላይ ነው፡፡ ከ ሲ ኤም ሲ በመገናኛ መስቀል አደባባይ ያለው መስመር በተመሳሳይ ሁኔታ የሀዲድ ዝርጋታው ተጠናቋል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሜክሲኮ ጦር ሀይሎች ያለው መስመር የድልድዮች ግንባታ አልቆ ሀዲድ የማንጠፍ ስራ እየተስራ ነው ብለዋል፡፡ ሙሉ የባቡሩ ስራም በ2007 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ተጠናቅቆ ስራ ይጀምራል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የባቡር ስራውን ለቻይናው ‘ቻይና ሲ ኤን አር ቻንግቹን ሬልዌይ ቪሄክልስ’ ኩባንያ የሰጠው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ሲሆን ኩባንያውም እስከ ጥር ወር 2007ዓ.ም ሁሉንም ባቡሮች አጠናቆ ለማስረከብ ተዋውሎ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ነጭ እና አረንጓጌ ቀለም እንደሚኖረው የተገለጸው ባቡር በሰዓት 70 ኪሎ ሜትሮች የመጓዝ አቅም ያለው ሲሆን ለተሳፋሪዎች ምቹ በሆነና የጸሀይ ብርሃንን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ ዲዛይን መደረጉን እነዚሁ ባለስልጣኖቹ ጨምረው ገልጸዋል:: ከዚህ አዲስ የመጓጓዣ ቴክኖሎጂ ጋር ለመተዋወቅም በመጪው መስከረም ወር 50 ኢትዮጲያዊያን የባቡር አሽከርካሪዎችንና የጥገና ሰራተኞችን ወደ ቻይና በመላክ ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በእርግጥ ይህ ከፍተኛ የሆነ መዕዋለ ነዋይ ፈስቦት በመስራት ላይ ያለው ይህ ቀላል የከተማ ባቡር በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን ረጃጅም የትራንስፖርት ሰልፍ ያስቀራልን? ከጥቂት ወራት በኋላ የባቡሩ ስራ ተጠናቅቆ ሙሉ ለሙሉ ስራ ሲጀምር መልስ ይሰጠናል፡፡ አንባቢዎች ስለዚህ የባቡር ፕሮጀክት ያላችሁን አስተያዬት ከዚህ በታች ሊተው ይችላሉ::
The post የመጀመሪያው እና በኤሌክትሪክ የሚሰራው ባቡር በቀጣዩ ወር አዲስ አበባ ይገባል appeared first on AddisNews.net.