Quantcast
Channel: Travel – AddisNews.net
Viewing all articles
Browse latest Browse all 38

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቦላ ወደተስፋፋባቸው አገሮች የሚያደርገውን በረራዎችን አቋረጠ

$
0
0
  • አስካይ አየር መንገድ በሽታው ወደተስፋፋባቸው አገሮች የሚያደርጋቸውን በረራዎች አቋረጠ
  • የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ልዩ ጥንቃቄ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጿል

( ሪፖርተር ) – የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም የጤና ድርጅት በአንደኛ ደረጃ ቫይረሱ እጅግ የተስፋፋባቸው አገሮች በማለት የዘረዘራቸው ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያና ጊኒ የቀጥታ የበረራ አገልግሎት ስለሌለው ለበሽታው የተጋለጡ መንገደኞች እንደማያጓጉዝ አስታወቀ፡፡

አየር መንገዱ የኢቦላ ቫይረስ እንዳይስፋፋ እየወሰደ ስላለው የጥንቃቄ ዕርምጃዎች አስመልክቶ ለመንገደኞችና ለደንበኞቹ ባሠራጨው መልዕክት ቫይረሱ የተስፋፋባቸው ሦስቱ አገሮች የቀጥታ በረራ አገልግሎት የማይሰጥ ቢሆንም፣ አየር መንገዱ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ልዩ የጥንቃቄ ዕርምጃ እየወሰደ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

የቫይረሱ ሥርጭት እንደሚኖር የሚጠረጠርባቸው አገሮች በረራ በሚደረግበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኞች ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ ሊደረጉ የሚገቡ ቅድመ ጥንቃቄዎችን በተመለከተ ለመንገደኞች አስፈላጊውን መረጃ እንደሚሰጥ፣ የአንዳንድ አገሮች የጤና ፖሊሲ በሚጠይቀው መሠረት መንገደኞች አውሮፕላን ከማረፉ በፊት የጤንነት ሁኔታቸውን በተመለከተ የተዘጋጁ ፎርሞች እንዲሞሉ እንደሚያደርግ፣ መንገደኞች ወደ አውሮፕላኖች ከመሳፈራቸው በፊት የዓለም የጤና ድርጅት፣ የዓለም የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት እንዲሁም የዓለም የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ያወጡዋቸውን መመርያዎች ለመተግበር ከእያንዳንዱ አገር የጤና አካላት ጋር በመተባበር እየሠራ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

Ethiopian_Airline_Fleet

በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች ወቅት የበረራ ላይ ሠራተኞች ከማንኛውም ዓይነት የሰውነት ፈሳሾች ጋር ንክኪ እንዳይኖራቸው በቂ ሥልጠና እንደተሰጣቸው፣ እንዳስፈላጊነቱ የሚጠቀሙባቸው የመከላከያ ቁሳቁሶች (የእጅ ጓንት፣ የሰውነት ማፅጃ ፈሳሽና ጭምብል) እንደተሰጣቸው፣ የበረራ ላይ ሠራተኞች የመንገደኞችን ሁኔታ በንቃት እንዲከታተሉና የሚያጠራጥር መንገደኛ ካጋጠማቸው ወዲያውኑ ሪፖርት እንዲያደርጉ መደረጉን ገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ስለሚደረጉ ጥንቃቄዎች በተመለከተ ከተጠረጠሩ አገሮች የሚመጡ አውሮፕላኖች ተነጥለው በተዘጋጀላቸው ማቆሚያ እንዲቆሙና መንገደኞቹም በተዘጋጀላቸው የተለየ በር ወደ ተርሚናል እንዲገቡ መደረጉን፣ ለብቻ በተዘጋጀላቸው በር የገቡት መንገደኞች ላይ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የመጡ የጤና ባለሙያዎች የጤና ምርመራ በማድረግ ላይ መሆናቸውን፣ አውሮፕላኖቹም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና የጤና ባለሙያዎች ባስቀመጡት መሥፈርት መሠረት እንደሚፀዱ አስታውቋል፡፡ እንዲሁም ሁሉም የአየር መንገዱ ሠራተኞች፣ የደኅንነት አካላት፣ የኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪዎችና ሌሎችም አዲስ አበባ ኤርፖርት የሚሠሩ ሠራተኞች በሙሉ ስለበሽታው መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች በቂ ማብራሪያ እንደተሰጠ አየር መንገዱ አስረድቷል፡፡

አየር መንገዱ፣ ‹‹እስካሁን ድረስ አንድም በቫይረሱ የተያዘ ሰው አዲስ አበባ ኤርፖርት ባይገኝም፣ ሁሉንም የኤርፖርት ሠራተኞችና በከተማው ውስጥ የሚገኙ ሆቴሎች የበሽታው ምልክት ቢታይና የሚያጠራጥር ሁኔታ ቢኖር እንዴት መቆጣጠር እንደሚችሉ በቂ ገለጻ ተሰጥቷል፤›› ብሏል፡፡

በሽታው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይዛመትና ተገቢው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ በአገር አቀፍ ደረጃ በተቋቋመውና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሚመራው ብሔራዊ ኮሚቴ ውስጥ አየር መንገዱ አባል በመሆን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞቹንና የሠራተኞቹን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ በቀጣይነት ሁኔታዎችን በመከታተል፣ ተጨማሪ ዕርምጃዎች ካስፈለጉ ወይም የሚመለከታቸው ብሔራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት የመፍትሔ ሐሳቦች ካቀረቡ ተጨማሪ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያና ጊኒ ባይበርም፣ በምዕራብ አፍሪካ አገሮች ናይጄሪያን ጨምሮ በርካታ የበረራ መዳረሻዎች አሉት፡፡ በናይጄሪያ 13 ሰዎች በኢቦላ ቫይረስ የተጠቁ ሲሆን አራቱ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በ189 ሰዎች ላይ ክትትል እየተደረገ እንደሆነና የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን የናይጄሪያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

እንደ ብሪቲሽ ኤርዌይስና ኤምሬትስ ያሉ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ወደ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ የሚያደርጓቸውን በረራዎች ቀደም ሲል ያቋረጡ በመሆናቸው፣ ኬንያ ኤርዌይስ ወደእነዚህ አገሮች የሚያደርገውን በረራዎች ከነሐሴ 13 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚያቋርጥ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም መነሻቸው ከሴራሊዮን፣ ከጊኒና ከላይቤሪያ የሆኑ መንገደኞችን ወደ ግዛቷ እንደማታስገባ ኬንያ አስታውቃለች፡፡

በምዕራብና በመካከለኛው አፍሪካ በርካታ መዳረሻዎች ያሉትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሸሪክ ኩባንያ የሆነው አስካይ አየር መንገድ ወደ ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያና ጊኒ የሚያደጋቸውን በረራዎች ከሐምሌ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ አቋርጧል፡፡ በምዕራብና በመካከለኛው አፍሪካ 22 መዳረሻዎች ያሉት አስካይ አየር መንገድ ከክልሉ የሰበሰባቸውን መንገደኞች ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያቀብል አየር መንገድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአስካይ ላይ የ45 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ አለው፡፡

አስካይ፣ ኬንያ ኤርዌይስ፣ ብሪቲሽ ኤርዌይስና ኤምሬትስ ወደ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ የሚያደርጉትን በረራዎች ያቋረጡ ቢሆንም ወደ ናይጄሪያ የሚያደርጓቸውን በረራዎች ቀጥለዋል፡፡ ሉፍታንዛ፣ ኤምሬትስ፣ ኳታር ኤርዌይስና ኤርፍራንስ የመሳሰሉ ታዋቂ አየር መንገዶች ወደ ናይጄሪያ በመብረር ላይ ናቸው፡፡

ተጨማሪውን ከሪፖርተር ያንብቡ Ethiopian Reporter

The post የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቦላ ወደተስፋፋባቸው አገሮች የሚያደርገውን በረራዎችን አቋረጠ appeared first on AddisNews.net.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 38

Trending Articles